ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አንተ አልህ ብሎ መለሰለት። የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። ጲላጦስም ደግሞ። አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። ጲላጦስም። የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። ፲፩የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። ፲፪ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ። እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። ፲፫እነርሱም ዳግመኛ። ስቀለው እያሉ ጮኹ። ፲፬ጲላጦስም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን። ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። ፲፭ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ፲፮ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ፲፯ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ ፲፰የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ፲፱ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ፳፩አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ፳፪ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። ፳፫ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ፳፬ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። ፳፭በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። ፳፮የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። ፳፯ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። ፳፰መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። ፳፱የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። ፴፩እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ። ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ ፴፪አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። ፴፫ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፴፬በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። ፴፭በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። ፴፮አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። ፴፯ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። ፴፰የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። ፴፱በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። ፵-፵፪አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ፥ ፵፫እርሱም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ፵፬ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው፤ ፵፭ከመቶ አለቃውም ተረድቶ በድኑን ለዮሴፍ ሰጠው። ፵፮በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው፥ በመቃብሩ ደጃፍም ድንጋይ አንከባለለ። ፵፯መግደላዊትም ማርያም የዮሳም እናት ማርያም ወዴት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።