ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥ በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤ አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥ ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። ፲፩በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና። ፲፪ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት። ፲፫ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። ፲፬እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። ፲፭ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። ፲፮ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። ፲፯ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። ፲፰ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። ፲፱ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን። ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ። ፳፩ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ። ፳፪ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና። ፳፫ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። ፳፬ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። ፳፭ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ፳፮ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ ፳፯የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች። ፳፰ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። ፳፱ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ። ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። ፴፩ደቀ መዛሙርቱም። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ። ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። ፴፪ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። ፴፫ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። ፴፬እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት። ፴፭እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት። ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። ፴፮ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ። እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። ፴፯ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ፴፰ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ ፴፱ገብቶም። ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። ፵፩የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። ፵፪ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። ፵፫ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው። የምትበላውን ስጡአት አላቸው።