በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት። ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ። የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ። ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ፲-፲፪ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። ፲፫በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። ፲፬መጥተውም። መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት። ፲፭እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ። ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው። ፲፮እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም። የቄሣር ናት አሉት። ፲፯ኢየሱስም መልሶ። የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። ፲፰ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት። ፲፱መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ ፳፩ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ፳፪ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። ፳፫ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? ፳፬ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? ፳፭ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም። ፳፮ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? ፳፯የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ። ፳፰ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ። ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። ፳፱ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ፴፩ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ፴፪ጻፊውም። መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ ፴፫በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። ፴፬ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ። አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ፴፭ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ። ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? ፴፮ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። ፴፯ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። ፴፰-፵የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። ፵፩ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ ፵፪አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ፵፫ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ። እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ፵፬ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።