፩እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤ ፪በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ፫ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። ፬የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ፭ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና። ፮ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም። ፯ኢየሱስም ደግሞ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። ፰ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። ፱በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። ፲ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ፲፩መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ፲፪እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ፲፫ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። ፲፬-፲፮ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። ፲፯ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። ፲፰እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ። ፲፱እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ። ፳ከእነርሱም ብዙዎች። ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ። ፳፩ሌሎችም። ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ። ፳፪በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ ፳፫ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። ፳፬አይሁድም እርሱን ከበው። እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት። ፳፭ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ ፳፮እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። ፳፯በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ ፳፰እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። ፳፱የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። ፴እኔና አብ አንድ ነን። ፴፩አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ፴፪ኢየሱስ። ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። ፴፫አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። ፴፬ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? ፴፭መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ ፴፮የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? ፴፯እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ፴፰ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ። ፴፱እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ። ፵ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ። ፵፩ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው። ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ። ፵፪በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።