፩ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። ፪የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። ፫እንግዲህ ወንድሞቹ። ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ፬ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት። ፭ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና። ፮ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። ፯ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል። ፰እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም። ፱ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። ፲ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። ፲፩አይሁድም። እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። ፲፪በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር። ፲፫ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። ፲፬አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። ፲፭አይሁድም። ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር። ፲፮ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፲፯ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ፲፰ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። ፲፱ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ፳ሕዝቡ መለሱና። ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል? አሉት። ፳፩ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። ፳፪ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። ፳፫የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? ፳፬ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። ፳፭እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? ፳፮እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? ፳፯ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም። ፳፰እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር። እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ ፳፱እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ ብሎ ጮኸ። ፴ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። ፴፩ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን? አሉ። ፴፪ፈሪሳውያንም ሕዝቡ ሰለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ። ፴፫ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ። ፴፬ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ። ፴፭እንግዲህ አይሁድ። እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን? ፴፮እርሱ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው? ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ፴፯ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። ፴፰በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ፴፱ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። ፵ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ። ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤ ፵፩ሌሎች። ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤ ሌሎች ግን። ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? ፵፪ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን? አሉ። ፵፫እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ ፵፬ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም። ፵፭ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም። ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው? አሉአቸው። ፵፮ሎሌዎቹ። እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ። ፵፯እንግዲህ ፈሪሳውያን። እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ፵፰ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ፵፱ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው። ፶ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ። ፶፩ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። ፶፪እነርሱም መለሱና። አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። ፶፫እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።