፩ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። ፪እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን። ፫ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። ፬ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። ፭ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? ፮በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። ፯መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። ፰የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። ፱የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። ፲በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። ፲፩እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ፲፪ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። ፲፫የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። ፲፬በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። ፲፭የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። ፲፮ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም። ፲፯ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ። ፲፰ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን። ፲፱ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። ፳የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። ፳፩ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።