ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ። ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል። ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት። ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል። በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤ ፲፩ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና። ፲፪ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ፲፫አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ፲፬አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ። ፲፭-፲፯ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። ፲፰ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን። ፲፱ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ። እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። ፳፩እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም። ፳፪ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ፳፫ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። ፳፬እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። ፳፭እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው። ፳፮ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። ፳፯እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። ፳፰አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። ፳፱ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።