፩ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። ፪የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና። ፫እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ፬አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? ፭ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ፮ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ፯ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። ፰የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። ፱እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። ፲ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ፲፩ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። ፲፪ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። ፲፫ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ ፲፬ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። ፲፭እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ ፲፮በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። ፲፯በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ፲፰ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። ፲፱እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። ፳እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። ፳፩የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። ፳፪ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ፳፫ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። ፳፬እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። ፳፭እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። ፳፮መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። ፳፯ኢየሱስም። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና። ፳፰ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ፳፱ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። ፴ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ፴፩እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ፴፪ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም። ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ፴፫ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና። ፴፬ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። ፴፭ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና። ፴፮አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። ፴፯መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? ፴፰ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ፴፱ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። ፵ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። ፵፩ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ፵፪ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። ፵፫ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። ፵፬አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ፵፭መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ ፵፮እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። ፵፯በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። ፵፰ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? ፵፱በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። ፶ሁሉም ትተውት ሸሹ። ፶፩ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ ፶፪ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ። ፶፫ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ፶፬ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። ፶፭የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ ፶፮ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። ፶፯-፶፱ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። ፷ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። ፷፩እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ፷፪ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። ፷፫ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? ፷፬ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። ፷፭አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። ፷፮ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ ፷፯ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። ፷፰እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። ፷፱ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። ፸እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። ፸፩እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ፸፪ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።