፩በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። ፪ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ ፫እየቀረቡም። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር፤ ፬በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም ደግሞ ወደ ውጭ ወጥቶ። እነሆ፥ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ አላቸው። ፭ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ። ፮ጲላጦስም። እነሆ ሰውዬው አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት አላቸው። ፯አይሁድም መልሰው። እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት። ፰ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤ ፱ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን። አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም። ፲ስለዚህ ጲላጦስ። አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? አለው። ፲፩ኢየሱስም መልሶ። ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው። ፲፪ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ። ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ። ፲፫ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ። ፲፬ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም። እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው። ፲፭እነርሱ ግን። አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። ንጉሣችሁን ልስቀለውን? አላቸው። የካህናት አለቆችም። ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ብለው መለሱለት። ፲፮ስለዚህ በዚያን ጊዜ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው። ፲፯ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ። ፲፰በዚያም ሰቀሉት፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በዚህ አንዱን በዚያ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ። ፲፱ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም። የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚል ነበረ። ፳ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር። ፳፩ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን። እርሱ። የአይሁድ ንጉስ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ አሉት። ፳፪ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ። ፳፫ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። ፳፬ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። ፳፭ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ፳፮ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ፳፯ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ፳፰ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ። ፳፱በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። ፴ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። ፴፩አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። ፴፪ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ ፴፫ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ ፴፬ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ። ፴፭ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል። ፴፮ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። ፴፯ደግሞም ሌላው መጽሐፍ። የወጉትን ያዩታል ይላል። ፴፰ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። ፴፱ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። ፵የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። ፵፩በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፥ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ። ፵፪ስለዚህ መቃብሩ ቅርብ ነበረና ስለ አይሁድ ማዘጋጀት ቀን ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።