ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። ስለዚህ እኅቶቹ ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል ብለው ወደ እርሱ ላኩ። ኢየሱስም ሰምቶ። ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ። ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት። ኢየሱስም መልሶ። ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው። ፲፩ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ። ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። ፲፪እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። ፲፫ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። ፲፬እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ። አልዓዛር ሞተ፤ ፲፭እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው። ፲፮ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት። ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ። ፲፯ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ፲፰ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ፲፱ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ፳፩ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ ፳፪አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው። ፳፫ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት። ፳፬ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው። ፳፭ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ፳፮ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት። ፳፯እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው። ፳፰ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ። መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት። ፳፱እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ፴፩ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ፴፪ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው። ፴፫ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ ፴፬ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት። ፴፭ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ፴፮ስለዚህ አይሁድ። እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ። ፴፯ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ። ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ። ፴፰ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ፴፱ኢየሱስ። ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው። ኢየሱስ። ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት። ፵፩ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ። አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ፵፪ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ። ፵፫ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ። አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። ፵፬የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም። ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው። ፵፭ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ፵፮ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። ፵፯እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው። ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። ፵፰እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ። ፵፱በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። ፶፩ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ፶፪ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። ፶፫እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። ፶፬ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። ፶፭የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። ፶፮ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በመቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው። ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን? ተባባሉ። ፶፯የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቀው ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው አዘው ነበር።