፩እንግዲህ። ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ ፪-፬በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። ፭ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ ፮በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። ፯ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም። ውኃ አጠጪኝ አላት፤ ፰ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ፱ስለዚህ ሳምራዊቲቱ። አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ፲ኢየሱስ መልሶ። የእግዚአብሔርን ስጦታና። ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። ፲፩ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? ፲፪በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። ፲፫ኢየሱስም መልሶ። ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ ፲፬እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። ፲፭ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው። ፲፮ኢየሱስም። ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት። ፲፯ሴቲቱ መልሳ። ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ። ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ ፲፰አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት። ፲፱ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። ፳አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ፳፩ኢየሱስም እንዲህ አላት። አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። ፳፪እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ፳፫ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ ፳፬እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ፳፭ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ፳፮ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። ፳፯በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም። ፳፰ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም። ፳፱ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች። ፴ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ፴፩ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት። ፴፪እርሱ ግን። እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው። ፴፫ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ። የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ። ፴፬ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። ፴፭እናንተ። ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። ፴፮የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። ፴፯አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። ፴፰እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ። ፴፱ሴቲቱም። ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት። ፵የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ። ፵፩ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ፵፪ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር። ፵፫ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። ፵፬ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። ፵፭ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። ፵፮ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። ፵፯እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። ፵፰ስለዚህም ኢየሱስ። ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው። ፵፱ሹሙም። ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው። ፶ኢየሱስም። ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። ፶፩እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና። ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት። ፶፪እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም። ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት። ፶፫አባቱም ኢየሱስ። ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ። ፶፬ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።