በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ፲፩ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። ፲፪ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ። ፲፫የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ፲፬በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ ፲፭የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ፲፮ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። ፲፯ደቀ መዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ። ፲፰ስለዚህ አይሁድ መልሰው። ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት። ፲፱ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። ፳፩እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። ፳፪ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ። ፳፫-፳፭በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤