፩-፫በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ ፭-፯ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። ፲፩ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። ፲፪ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤ ፲፫ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ። ፲፬ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና። ፲፭የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ ፲፮ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ፲፯ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና። ፲፰ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤ ፲፱ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ፤ እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት የምትለውን ትእዛዝ ሊታገሡ አልቻሉምና፤ ፳፩ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ ፳፪ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ ፳፫በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ ፳፬የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። ፳፭ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ፳፮በዚያም ጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጠ፥ አሁን ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። ፳፯ዳሩ ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል፥ የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል። ፳፰ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ ፳፱አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።