፩-፫በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። ፬ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። ፭ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ፮ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት። ፯ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ። ፰ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው። ፱ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤ ፲ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል። ፲፩ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል፤ በክርስቶስ ላይ ተነሥተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና፤ ፲፪የፊተኛውንም እምነታቸውን ስለ ናቁ ይፈረድባቸዋል፤ ፲፫ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም። ፲፬እንግዲህ ቆነጃጅት ሊያገቡ፥ ልጆችንም ሊወልዱ፥ ቤቶቻቸውንም ሊያስተዳድሩ፥ ተቃዋሚውም የሚሳደብበትን አንድን ምክንያት ስንኳ እንዳይሰጡ እፈቅዳለሁ፤ ፲፭ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን እንዲከተሉ ፈቀቅ ብለዋልና። ፲፮ባልቴቶች ያሉት የሚያምን ቢሆን ወይም የምታምን ብትሆን፥ ይርዱአቸው፥ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞችን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት። ፲፯በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። ፲፰መጽሐፍ። የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ። ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና። ፲፱ከሁለት ወይም ከሦስት ምስክር በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። ፳ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሰሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው። ፳፩አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ። ፳፪በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፥ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ። ፳፫ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ። ፳፬የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤ ፳፭እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፥ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም።