፩ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። ፪እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ ፫የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ፬ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ፭ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? ፮በትዕቢት ተነፍቶ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። ፯በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል። ፰እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ ፱ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ፲እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፥ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። ፲፩እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፥ የማያሙ፥ ልከኞች፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ፲፪ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። ፲፫በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ። ፲፬ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። ፲፭ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። ፲፮እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።