፩ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። ፪የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ፫ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። ፬ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። ፭እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። ፮እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን። ፯ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፰ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። ፱በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፲ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ፲፩ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። ፲፪እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። ፲፫ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። ፲፬እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን። ፲፭ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። ፲፮እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። ፲፯በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና። ፲፰ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። ፲፱እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። ፳ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? ፳፩እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።